16 September 2020 Written by 

በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን በመከላከል ረገድ የማኅበራዊ ሚዲያ አዉታሮች ሚና - ክፍል 1

 

 

“The evangelists of hate and division are wreaking havoc in our society using social media.”

Prime Minister Abiy Ahmed, Nobel Lecture, 11 December 2019

 

መግቢያ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጥላቻ ንግግር በኢትዮጵያ በዓይነትም በስፋትም እየጨመረ እና እየሰፋ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚጠቀሰው አንዱ ምክንያት የማኅበራዊ ሚዲያ አዉታሮች በጊዜና በፍጥነት ይዘትን ባለማረማቸው (absence of effective content moderation) ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ የተዘጋጀው አዲስ ዘይቤ ሚዲያ ሸንጎ ግሎባል ከተሰኘ ውጥን ጋር በመሆን ነሀሴ 29፣ 2012 ዓ.ም. በበይነ መረብ አማካኝነት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ለንግግር መነሻነት የቀረበ ምልከታ ነው፡፡

የዚህ ጽሁፍ ዓላማም የጥላቻ ንግግር ጽንሰ ሃሳቡን በአጭሩ ማብራራት፣ አዲሱ የጥላቻ ንግግር መከላከያ አዋጅ ተስፋና ስጋት፣ የእኩልነት ፍ/ቤት ወይም ችሎት ማቋቋም አስፈላጊነት፣ ስለ ይዘት እርማት በዘርፋ ያሉ የሌሎች አገራትን ልምድ ለመጠቆም ፤ እንዴት የሰብዓዊ መብት ተኮር ዘዴ (Human rights based approach) ጠቃሚ እንደሆነ ለማሳየት እና ለወደፊቱ ምን ይደረግ በሚለው ጉዳይ ምክረ ሃሳቦችን መጠቆም ናቸው፡፡

የጥላቻ ንግግር ሰዎች በያዙት ማንነት (የብሄር፣ ጾታ፣ ሃይማኖት ) እንዲገለሉ፣ እንዲጠሉ ወይም ጥቃት እንዲደርስባቸው የሚያደርግ ንግግር ነው፡፡ የዓለምአቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 20 (1) ላይ አገራት የጦርነት ቅስቀሳ የሚሰብኩ የጥላቻ ንግግሮችን በህግ እንዲከለክሉ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ የተ.መ.ድ. ሰብዓዊ መብት ኮሚቴም ይህንን በተመለከተ በሰጠው ጠቅላላ አስተያየት ቁ.11/1983 የጦርነት ቅስቀሳ ሲባል ከተ.መ.ድ ቻርተር በተጻረረ መልኩ ማነኛውም ዓይነት አሳሳች ውሸት ( propaganda) ሆኖ ወረራን ወይም ሰላምን የሚያሰጋ ንግግር ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያም የጥላቻ ንግግር ስጋት ለመቀነስ በሚል በ2012ዓ.ም. ራሱን የቻል አዋጅ አጽድቃለች፡፡ በእርግጥ በህግ መከላከል (legislative intervention) አንዱ መንገድ ቢሆንም ሌሎች ቅጣት አላባ ዜዴዎችን (non-punitive measures) እንደ ይዘት ይታረምልኝ (content moderation)፣ ብዙ ንግግርን በመፍቀድ እና የሚዲያ ትምህርት (media literacy) በተጓዳኝ በመውሰድ መካላከል እንደሚቻል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

1. የጥላቻ ንግግር ጽንሰ ሃሳቦች አጭር ምልከታ

 

የጥላቻ ንግግር ሁሉን አቀፍ ትርጓሜ ወይም ብያኔ አልተሰጠውም ለምን ቢባል ጥላቻ ከስሜት የሚመነጭ ጽንሰ-ሃሳብ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግርን ብያኔ ለመስጠት ከባድ ነው፡፡ ብያኔ ሲሰጠውም እንደየአገራቱ ሁኔታ፣ አውድ እና ምሳሌ ይወሰናል፡፡ ለዚህም ይመስላል አንድ የአሜሪካ ፍ/ቤት ዳኛ ስቴዋርት ስለ አስጸያፊ ንግግሮችን (obscenity) በሰጠው የፍርድ አስተያየት እንዲህ ይላል ፦ “የማውቃቸው፣ ሳያቸው ነው (“I know it when I see it.”) ሲል በጃኮቢሊስ እና ኦሃዮ  መካከል በነበረው ክርክር አስፍሯል፡፡ የጥላቻ ንግግሮችን ደግሞ ዳኛ ስቴዋርት ካለው በላይ ማንነታቸውን ለማወቅ ከባድ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡

     የጥላቻ ንግግር የሰውን ልጅ ክብር እና ኩራት የሚያዋርድ ተግባር ነው፡፡ ፕ/ር ጀረሚ፡ ዋልዶርን ‘The Harm in Hate Speech’ በሚለው መጽሃፋቸው ላይ የጥላቻ ንግግር የሰውን ልጅ ክብር የሚጎዳ በተለይም ልዩ መገለጫ በመለጠፋ ለምሳሌ የቆዳ ቀለሙ፣ ብሄሩ እና ሃይማኖቱን መሠረት አድርጎ ከማህበረሰቡ ለመንጠል እና ያላቸውን መልካም ገጽታ በማጉደፍ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በተለይም የጥላቻ ንግግር በጽሁፍም፣ በምስል ወይም በድምጽ ሲነገር ቢያንስ ሁለት መልዕክትን በህብረተሰቡ ዘንድ ያስተላልፋል፡፡ የመጀመሪያው የጥላቻ ንግግር ተጠቂውን ቡድን ከሰውነት እርከን ያወረደዋል (dehumanise)ብሎም ከሰውነት ተርታ እንዲወርድ ያደርገዋል፡፡ ሌላው ደግሞ በአጥቂ ወገን የራስን ቡድን በስጋት ውስጥ እንዳለ በመቁጠር ሌሎች የቡድኑ አባላት የጥላቻ ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ ሊያደርግ ይችላል፡፡ (ጀረሚ፡ዋልዶርን፡ 2012፡5)

     የጥላቻ ትርጉምንም በሚመለከት በ ኔልሰን ማንዴላ ፍውንዴሽን እና አፍሪ ፎረም መካከል በነበረ አንድ ክርክር የደቡብ አፍሪካ የእኩልነት ፍ/ቤት እኤአ በ2019 ዓ.ም የጥላቻ ንግግርን ለቃሉ በሚሰጠው ሰዋሰዋዊ ትርጉም (grammatical meaning) መተርጎም እንዳለበት አቅጣጫ ጠቁሟል፡፡ Hate speech means a “speech that expresses hatred towards a person or his or her group based on race or other attributes such as religion, sex, ethnicity, sexual orientation and the like.” በዚህም መሠረት የጥላቻ ንግግር ማለት የሌሎችን ሃይማኖትን፣ ጾታን፣ ጎሳን እና መሰል ነግሮችን መሠረት በማድረግ ቡድኖችን እንዲጠሉ ማድረግ ነው ሲል ፍርዱን አስቀምጧል፡፡ (የፍርዱ አንቀጽ 94 ይመለከቷል፡፡ )

     በ ማርክ ኖርውድ እና የእንግሊዝ መንግስት መካከል በነበረ ክርክር የእንግሊዝ ብሄራዊ ፓርቲ ቀኝ አክራሪ አስተባባሪ የነበረው  ማርክ፡ ኖሩድ ከመኖሪያ ቤቱ መስኮት ላይ “እስልምና ከእንግሊዝ ይውጣ፣ የእንግሊዝን ህዝብ እንጠብቅ”/ “Islam out of Britain – Protect the British People የሚል እንዲሁም ከመስከረም 11 የአሜሪካ መንትያ ህንጻ በአሳት መያያዝ የሚገልጽ ብሎም ጨረቃን እና ኮከብን ምስል ላይ የክልከላ ምልክት ያለበት ትልቅ ፖስተር ሰቅሎ” ነበር፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ፍ/ቤትም እንዲህ መሰል የቃላትና ምስል ጥላቻ በእንግሊዝ አገር በሚኖሩ ሙስሊሞች ላይ ጥቃት የሚከፍት ነው ብሎም ሃይማኖቱን ከሽብርተኝነት ጋር ማገናኘት ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብት እሴት ጋር የማይሄድ፣ ማኅበራዊ ሰላምን እና መቻቻልን የሚሸረሽር እንደሆነ በፍርዱ አቀምጧል፡፡

     በሌላ ጉዳይም አንድ የደቡብ አፍሪካ እኩልነት ፍ/ቤት፣ በ አፍሪ ፎረም እና ጁሊየስ፡ ማሌማ መካከል በነበረ ክርክር ተከሳሹ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ህዳጣን ቡድኖች ላይ በደቡብ አፍሪካ የነጻነት ወቅት ሲዘፈኑ ከነበሩ የትግል ዘፈኖች ውስጥ አንድ አዝማች ግጥም መዞ “shoot the Boers/farmers they are rapists/robbers” “ቦሆርስን/ገበሬዎችን ግደሏቸው ፤ ደፋሪና ዘራፊ ናቸው”፡፡ ፍ/ቤቱም የቀድሞ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (African National Congress-ANC) አባል የአሁኑ የኢኮኖሚ ነጻነት ታግይ መሪ ጁሊየስ፡ ማሌማ የዘፈነው ዘፈን የጥላቻ ንግግር ነው በማለት ወስኗል፡፡ በተለይም ይህ ንግግር የነጭ ገበሬዎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል አግላይ በመሆኑ በህዝብ በተሰበሰበበትም ሆነ በግል ስፍራ እንዳይዘፈን ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ (የፍርዱ አንቀጽ 120 ይመለከቷል፡፡)

በኢትዮጵያ ታሪክም የጥላቻ ንግግር አዲስ ጽንሰ ሃሳብ አይደለም፡፡ ለምሳሌ፦ የቆዳ ቀለማቸው ጠቆር ያሉ ሰዎችን በተለምዶው ባሪያ (slave) የሚል አገላለጽ ነበር፡፡ (ተሻለ፡ ጥበቡ፡ 1995፡58) አጼ ሃ/ስላሴ ጀምሮ በተከታታይ የመጡ መንግስታትም ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ፖለቲካዊ ፍረጃ በማድረጋቸው የጥላቻ ንግግር እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ ጠባብ፣ ትምክህተኛ እና ነፍጠኛ የሚሉ ቃላትን በተለያዩ አጋጣሚዎች የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ሲናገሩ ተስተዉሏል፡፡ (ዉብሸት፡ ሙላት፡2016) ለምሳሌ ፦ ነፋጠኛ የሚለው ቃል በቅርቡ ለደረሱ ጥቃቶች እንደ ኅቡዕ የፖለቲካ ማጥቂያ ቃል (dog whistle call) እንደዋለ መረዳት ይቻላል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግስቱ ከመጣ ጀምሮ፤ የጎሳ ፌዴራሊዝም የአገሪቱ ፖለቲካዊ ርዕዮት ሆኖ በመተከሉ ምክንያት፣ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ክልሎች ራስን በራስ የማስተዳድር መብት ቢያጎናጽፍም ፤ ጎሳ ላይ ማጠንጠኑ በአንድ ክልል ውስጥ አንድ ብሄር የበላይ ሌላው የበታችነት እንዲሰማው በማድረጉ የአገሪቱ ጥንተ አብሶ (original sin) እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ (ዮናታን፡ ተስፋየ፡ 2016፡ 232) በዚህ ረገድ የህገ መንግስቱን ህጽጽ  ፕ/ር ምናሴ፡ ሃይሌ እንደሚከተለው ተመልክቶታል፡፡ “የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የሶቬት ሞዴል ፌደሬሽን በመከተሉ ዘጠኝ የጎሳ ክልሎችን (tribal homelands) ፈጥሯል፡፡ ” ይህም በመሆኑ፣ ጎሰኝነት (ethnicity) በጣም ከመጠን በላይ ፓለቲካዊነት ስለተላበሰ እያንዳንዱ ጎሳ በሚኖርበት ክልል የበላይነት ስሜት እንዲኖር፤ ፍጹም የሃብት ባለቤትነት (exclusive ownership of resources)  እና ልዩ ልዩ የመብት ተጠቃሚነቶች እንዲኖር አስችሏል፡፡ በመሆኑም የፓለቲካ ሊሂቃን የጥላቻ ንግግር በመጠቀም “እኛ” (‘’us”) ‘’እነሱ” (“them”) የሚሉ ስሁት እና የተዛቡ ትርክቶችን በመንዛት በማህበረሰቡ ዘንድ ለዘመናት የነበረውን ማኅበራዊ ትስስር እና መስተጋብር አደጋ ላይ ጥለውታል፡፡ ለምሳሌ፦ “መጤ” እና “ሰፋሪ” የሚሉ የጥላቻ ቃላትን ማንሳት ይቻላል፡፡

ሌላው የህገ መንግስት ችግር፣ ህገ መንግስቱ በአንድ በኩል ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦችን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ቢያደርግም ፤ ጎሰኝነትን ተቋማዊ እና ህጋዊ እውቅና እንዲሰጠው በማድረጉ በተለያዩ ቦታዎች የ “ጨቋኝ - ተጨቋኝ ትርክት” በተግባር እንዲስፋፋ አድርጓል በዚህም ሳቢያ ጥላቻ እንዲስፋፋ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ፦ የሕገ መንግስቱ መግቢያ ላይ “ከታሪክ የወረስነው የተዛባ ግንኙነት” የሚለው አገላለጽ በተለይም በታሪክ አጋጣሚ አንድ ህዝብ ሌላውን እንደ ጨቆነ ተደርጎ እንዲታይ በማድረጉ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክትን ህጋዊ ሽፋን እንዲላበስ አድርጓል፡፡  ይህንንም በተመለከተ ኢትዮጵያን የጎበኙት የህዳጣን (minority) መብት ጉዳዮችን የሚከታተሉት የተ.መ.ድ. ልዩ ገለልተኛ ባለሙያ፣ ጋይ፡ማክዶጋል እኤአ በ 2006 ዓ.ም. ( UN Independent Expert on Minority Issues, Gay McDougallእንዲህ ብለው ነበር ፦

 

Self-determination is provided for in the creation of nine ethnically-based regional states of the federation, with the right to draft regional constitutions, to promulgate laws, to establish and administer government functions and to secede. (...) Ethnically-based federalism has served, however, to politicize ethnicity as the most salient individual and group marker, leading to new arenas, dynamics and dimensions of ethnic division, discrimination and exclusion.

 

ይህም ማለት የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ዘጠኝ የጎሳ መር ክልሎች እንዲፈጠሩ አስችሏል፣ የክልል ህገ መንግስቶች እንዲጻፋ አግዟል፣ ህግጋት እንዲወጡ ረድቷል፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል መብት አጎናጽፏል፡፡ ዳሩ ግን ይህ የጎሳ መር ፌዴራሊዝም ጎሳን ፓለቲካዊ ርዕዮት በማድረግ ፤ በጣም የተለየ የግል እና የቡድን መወሰኛ በማድረጉ ፤ የጎሳ (ብሄር) ክፍፍል፣ መድሎ እና የመገለል አዲስ አውድማ፣ መዘውር እና ገጽታ አምጥቷል፡፡ በዋናነትም የክልል ህገ መንግስታት ባመጧቸው አግላይ ድንጋጌዎች የተነሳ በህብረተሰቡ መካከል ‘መጤ’ እና ‘ነባር’ የሚል ክፍፍል እንዲወድቁ አስችሏል፡፡ ለምሳሌ፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግስት አንቀጽ 2 ብንመለከት በቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ነባር ህዝቦች በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦ እና ኮሞ ናቸው ሌሎች ደግሞ መጤ ናቸው ይላል እንዲሁም የሐረሪ ክልል ሕገ መንግስት በተመሳሳይ በአንቀጽ 8 የሐረሪ ህዝብ የክልሉ የበላይ ስልጣን ባለቤት ነው፡፡ ስልሆነም ይህ መዋቅራዊ አድሏዊ አሰራር ጥላቻን ተቋማዊ ቅርጽ እንዲኖረው አድርጓል፡፡

ከአሁን ቀደም ፌስቡክ በሮሂንጋ ሙስሊሞች በማይናማር መንግስት ወታደሮች እንዲጠቁ የሚቀሰቅሱ አደገኛ ንግግሮችን በፍጥነት ባለማንሳቱ ሰፊ ወቀሳ ሲሰነዝርበት ነበር፡፡ ይህንንም ጉዳይ በተ.መ.ድ ሰብዓዊ መብት ስር የተቋቋመው ገለልተኛ ዓለምአቀፍ የእውነት አጣሪ ልዑክ (the Independent International Fact-Finding Mission on Myanmar) በአንቀጽ 697 ላይ አረጋግጧል፡፡ የፌስቡክ ደርጅትም በሮሂንጋ ሙስሊሞች የደረሰውን ሰቆቃ በመከላከል ረገድ ድርጅቱ በቂ ስራ እንዳልሰራ አምኗል፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያም በወርሃ ሰኔ ማብቂያ ላይ ለተከሰቱ ብሄርን መሠረት ያደረገ እና ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች የጥላቻ ንግግር አንዱ ምክንያት ነበር፡፡ ለአብነትም የተ.መ.ድ. ሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ጽ/ቤት  (UN Office of the High Commissioner for Human Rights) ሰኔ 26፡ 2012 ዓ.ም.  ባወጣው መግለጫ ጥቃቶቹ  የብሄር ተኮር ጥቃት (ethnic based attacks) እንደነበሩ እና ግጭትን የሚያባብሱ አደገኛ ንግግሮች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ይህንንም በሚመለከት ዓለማአቀፍ የህዳጣን ተቆርቋሪ ቡድን (Minority Group International ባወጣው መግለጫ እንዲህ ሲል ለማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች በአጽንዖት መልዕክቱን አስፍሯል፡፡

 

Social media platforms including Facebook and Twitter to be on the alert for hate speech against minorities in Ethiopia and quickly take down harmful content that encourages inter-ethnic hatred and violence.

 

በአጭሩም የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች በተለይም ፌስቡክ እና ትዊተር በኢትዮጵያ በሚገኙ ህዳጣን (minorities) ጥቃት እንዳይደርስባቸው ንቁ መሆን እንዳለባቸው ፤ በዋናነትም አደገኛ እና ህዝብን ከህዝብ ሊያጋጩ የሚችሉ ይዘቶችን በፍጥነት ማውረድ እንዳለባቸው ጥሪ ቀርቧል፡፡

 

2. በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግር ለመከላከል የወጣው አዋጅ ቁ.1185/2012 ተስፋ እና ስጋቱ

 

የኢትዮጵያ የህዝብ ተ/ም/ቤት የካቲት 5፡ 2012 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የጥላቻ ንግግር እና ሃሰተኛ መረጃን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁ.1185/2012 በ23 ተቃውሞ፣ በ 2 ድምጸ ታዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁ ይታወሳል፡፡ አዋጁ የሚከተሉት ተስፋዎች ሲኖሩት በአንጻሩ ድግሞ ስጋቶችን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡

2.1.  ተስፋዎች

ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ የህጉን ረቂቅ ለምክር ቤት ባቀረቡብት ወቅት ይህንን ህግ ለማውጣት በቅን ልቡና ተመርተው እንደሆን ለም/ቤት አባላት የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ወቅት አስረድተዋል፡፡ በፓርላማ ውይይት ተገኝተው ገለጻ ያደርጉት ም/ጠ/ዐቃቢ ሕግ እንደገለጹት ከሆነ የጥላቻ ንግግር ዓላማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አደገኛ ንግግሮች በመበራከታቸው ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ አስነዋሪ እና ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች፣ የብሄር እና የሃይማኖት ጥቃቶች ብሎም መፈናቀሎችን በንጽሃን ላይ አስከትሏል፡፡ ይህንንም ለመግታት ብሎም የህግ የበላይነትን ለማስፈን በማሰብ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ምንም እንኳን የጥላቻ ንግግር የጸደቀበት ሂደት ጊዜ ትንሽ የጊዜ መጣደፍ ቢኖርም፤ አዋጁ በም/ቤት ውይይት ወቅት በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ አባላት ያቀረቡትን አስተያየቶች ከሞላ ጎደል አካቷል፡፡ ለምሳሌ፦ የኢትዮጵያ የዲጅታል መብቶች ቡድን ዝርዝር ምክረ ሃሳቦችን አቅረበዋል፡፡

     በመጀመሪያ ደረጃ የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል አንዱ መንገድ በጣም ሰብዓዊ መብቶችን በማይገድብ መልኩ ጠባብ ህግ ማውጣት ነው፡፡ ሁለተኛ አዋጁ የጥላቻ ንግግርን የተረጎመበት መንገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር በዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ህግ አረዳድ ሶስት ገጽታዎች አሉት፡፡ (ቶቢ፡ ሜንዴል፡ 2010፡ 4) አንደኛ ወንጀሉ ሆነ ተብሎ መፈጸሙ (intent/ mens rea) ነው፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ማነሳሳት (incitement) ነው፡፡ ሶስተኛው የተከለከሉ ተግባራት (prohibited acts) ማለትም ማጥቃት (violence/attack)፣ መድሎ (discrimination) እና ጥል (hatred) ናቸው፡፡ አዋጁም እነዚህን ቅደመ ሁኔታዎች በአካተተ መልኩ የጥላቻ ንግግርን በአንቀጽ 2 (2) ላይ እንደሚከተለው ደንግጎታል፦

 

የጥላቻ ንግግር ማለት በአንድ ሰዉ ወይም የተወሰነ ቡድን ላይ ያነጣጠረ፣ ብሄርን፡ብሄረሰብንና ህዝብን፣ ሀይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሠረት በማድረግ ሆነ ተብሎ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ ንግግር ነው።

 

ከእነዚህ በተጨማሪ አዋጁ ጥቅል ለሆኑ ቃላት ትርጉም ለመስጠት ሞክሯል፡፡ ለምሳሌ፦ መድሎ (discrimination) ማለት ብሔርን፣ ብሄረሰብን፣ ህዝብን፣ ሃይማኖትን፣ ዘርን፣ ፆታን፣ አካልጉዳተኝነትን ወይም ሌሎች በህግ የተጠበቁ ልዩነቶችን መሠረት በማድረግ የሚፈጸም የማግለል ተግባር እንደሆነ ከአንቀጽ 2 (5) ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ አንቀጽ 2 (6) ጥቃት (Violence) ማለት በግለሰብ ወይም በቡድን አባላት ንብረት፤አካል ወይም ሕይወት ላይ የሚፈጸም ጉዳት እንደሆነ ትርጉም ሰጥቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አዋጁ ጥላቻ ማሰራጨት ምን ማለት እንደሆነ በአንቀጽ 2 (7) ላይ ትርጉም ለመስጠት መክሯል፡፡ በዚህም መሠረት፦ ማሰራጨት” (dissemination) ሲባል ንግግርን በማናቸውም መንገዶች ለብዙ ሰዎች እንዲደርስ ማድረግ ሲሆን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይክ (like) ማድረግና ታግ (tag) ማድረግን እንደማያካትት ጠቁሟል፡፡

ሌላው በጣም በጥሩ ጎን ሊነሳ የሚችለው የማኅበራዊ ሚዲያ አዉታሮች ተጠያቂነትን በሚመለከት የተቀመጠው ጉዳይ ነው፡፡ በአንቀጽ 8 (2) ላይ  የማኅበራዊ ሚያዲያ አዉታሮች የጥላቻ ንግግርን  የተመለከተ ጥቆማ ሲደርሳቸው በሃያ አራት (24) ሰዓት ውስጥ ይህን መሰል ንግግሮችን ከአግልግሎት አውታራቸው ሊያስወግዱ እንደሚገባ ይጠቁማል። ይህም በመሆኑ ምክንያት ኢትዮጵያ የይዘት ይታረምልኝ ህግ (content moderation law) በማውጣት ቀዳሚ ከሚባሉ አገራት ተርታ ተሰልፋለች፡፡

 

2.2.   ስጋቶች

 

የጥላቻ ንግግር አዋጅ ሰብዓዊ መብቶች መክበር ላይ የሚከተሉትን ስጋቶች ይዞ መጥቷል፡፡ አንድም አዋጁ ለትርጉም አሻሚ እና ጥቅል ቃላትን መጠቀሙ ስጋት አጭሯል፡፡ በተለይም ጥል (hatred) የሚለውን ቃል ትርጉም አለመስጠቱ በህግ አተገባበር ወቅት አስፈጻሚው እንደፈለገ እንዳያውለው ስጋት አለ፡፡ በማርቀቁ ሂደት አማራጭ ረቂቅ ቀርቦ ህግ አውጭው ከካምደን መርሆች (Camden Principles ) ተሞክሮ እንዲውስዱ ምክረሃሳብ የቀረበ ቢሆንም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ የካምደን መርሆዎች ጥልን እንደሚከተለው ትርጉሞታል ፦ “hatred to mean to intense and irrational emotions of opprobrium, enmity and detestation towards the target group” ይህም ማለት ጥል በአንድ ቡድን ላይ የሚቃጣ ጥልቅ እና መሰረተ ቢስ የሆነ ከስሜት የሚመነጭ የወራዳነት፣ ጠላትነት እንዲሁም ጥላቻ ያዘለ ቃል ነው፡፡ አዋጁ ይህን ባለመከተሉ በተለይም በዓለምአቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR)  አንቀጽ 19 (3) ላይ የተቀመጠውን የህጋዊነት መርህ አያሟላም፡፡

     ሌላው በአንቀጽ 4 ላይ ጥላቻን ማሰራጨት የሚለው ሃረግ ምንም እንኳን አዋጁ ትርጉም ለመስጠት ቢምክርም፤ የቀረበበት መንገድ ለትርጉም ክፍት ነው፡፡ ለምሳሌ፦አንድ ሰው የሌላን ሰው ጥላቻ ንግግር በማኅበራዊ ሚዲያ አዉታሮች ገጽ ቢያጋራ (share)፣ በማሰራጨት ይጠየቃል? በዚህ ረገድ አውጁ ግልጽ አይደለም እንዳውም ማሰራጨት (dissemination) ከሚለው ቃል ይልቅ በዓለምአቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 20 (2) የተቀመጠው መወትወት (advocacy) የሚለው ቃል ቢጠቀም የተሻለ ነበር፡፡ ለምን ቢባል መወትወት ማሳብን ይገልጻልና፡፡

     አዋጁ በስፋት የሚተችበት ሌላኛው ጉዳይ፣ በዓለምአቀፍ ደረጃ የጥላቻ ንግግር ህግ ለማውጣት ይረዳ ዘንድ በተ.መ.ድ. ሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን በኩል የተዘጋጀውን የራባት መሪ ዕቅድ (Rabat Plan of Action) አለመከተሉ ነው፡፡ የራባት መሪ ዕቅድ ወደ ስድስት የሚደርሱ ቅድመ ሁኔታዎችን በመዘርዘር ያስቀምጣሉ፦

ሀ) የንግግሩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አውድ

ለ) በማህበረሰቡ ዘንድ የተናጋሪው ታዋቂነት

ሐ) ጉዳት ለማድረስ የሚደረግ የታወቀ አሳብ

መ) የንግግሩ ይዘት በተለይም ቆስቋሽ እና ቀጥተኛ መሆን

ሠ) የንግግሩ ታዳሚ ስፋት እና ተደራሽነት

ረ) ንግግሩ ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ አቅም ናቸው፡፡

 

የራባት መሪ ዕቅድን መሠረት ባደረገ መልኩ አማራጭ ረቂቅ የቀረበ ቢሆንም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ አዋጁ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች በለማካተቱ ፍ/ቤቶች የጥላቻ ንግግር ክስ ሲመጣላቸው የሚመለከቱበትን መነጸር እንዳያሰፋው ስጋት አጭሯል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ አዋጁ በመናገር ነጻነት ላይ አሸማቃቂ ውጤት (chilling effect) ይኖረዋል፡፡ በተለይም አዋጁ በአንቀጽ 7 (4) ላይ የእስራት እና የገንዘብ ቅጣትን ሊይዝ የሚችል ድንጋጌ አለው፡፡ በተለይም የጥላቻ ንግግር ከ 5,000 በላይ ተካታይ ባላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ አዉታሮች የሚጽፋ ሰዎች አማካኝነት ከተፈጸመ ከሶስት አመት ያለበለጠ ቀላል እስራት እና ከ100,000 (መቶ ሺ) ብር ያልበለጠ መቀጮ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህን ዓይነቱ የወንጀል ተጠያቂነት በማኅበራዊ ሚዲያ አዉታሮች በንቃት የሚጽፋ የማህብረሰብ አንቂዎችንና ጦማሪዎችን እንዳያሸማቅቅ ያሰጋል፡፡ በሌላ አገላለጽ ይህንን ቅጣት በመፍራት ግለሰቦች ሃሳባቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ አዉታሮች ከመግለጽ ሊቆጠቡ ይችላሉ፡፡ (ዮሐንስ፡ እንየው፡2020፡329)

 

3. የእኩልነት ፍ/ቤት ወይም መሰል ተቋማት ማቋቋም አስፈላጊነት

 

የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የወጣው አዋጅ በተቋማዊ አፈጻጸም ረገድ ሁለት ተቋማትን ለይቷል፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የአትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ናቸው፡፡ ሆኖም በሥራ ክትትል ረግድ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጥላቻ ንግግርን በሚመለከት እንዲሁም የብሮድካት ባለስልጣን ደግሞ የሃሰት ወሬዎችን በሚመለከት እንዲሰሩ በግልጽ ደንግጓል፡፡ አዋጁ አንቀጽ 8 (6) ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮችን የማዘጋጀት አላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይህም በሰብዓዊ መብት ቋንቋ መብቶችን የማስፋፋት (promotional mandate) እንጂ የመጠበቅ ተግባር (protection mandate) አይደለም፡፡

     የጥላቻ ንግግር መከላከያ አዋጅ በማስረጃ አደረጃጀት እና ክስ አሰማም ሂደት የተለየ ሥነ ሥርዓት ይዞ አልመጣም፡፡ በመሆኑም በመደበኛው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ይመራል ማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን ከመከላከል አንጻር በስፋት ጎልቶ የሚታየው ችግር የማስፈጸም እና የተሳሳተ የክስ ፍይል አከፋፈት ነው፡፡ በጥላቻ ንግግር ወይም የማንነት ጥቃት ከመክሰስ ይልቅ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለማናድ ወይም የፖለቲካ ቡድንን ማጥቃት የሚሉ ክሶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ (በእነ ኢ/ር ሃይሉ ሻውል መዝገብ አቶ በድሩ አደም የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የወንጀል ቁ.43246/99 ጉዳይ ይመለከቷል፡፡ ) (መሰንበት፡ አሰፋ፡ 2018፡36)  እንዲሁም የኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች የጥላቻ ንግግር ውሳኔ ሲሰጡ የሚከተሉት ዘዴ ንግግሩ የሚያስከትለውን ወጤት ሳይሆን (consequence based) የተባለው ነገር እውነትነት ላይ መሠረት (truth based defence) ያደረገ አካሄድ  ተከትለው ይወስናሉ፡፡ (ያሬድ፡ለገሰ፡ 2012፡365)

የጥላቻ ንግግርን በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል አንዳንድ አገራት ራሱን የቻለ ፍ/ቤት እና ችሎቶች ሰይመው በብቃት እየተከላከሉ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፦ ደቡብ አፍሪካ የጥላቻ ንግግርን የሚያይ የእኩልነት ፍ/ቤት (South African Equality Courts) አደራጅታለች፡፡ ደቡብ አፍረካ በታሪኳ የከፋ ዘርኝነት እና የጥላቻ ስርዓት (apartheid) አስተናግዳለች፡፡ ዜጎች ተከባብረው ለመኖር ጠንካራ ተቋም ማቋቋም መልካም ነው፡፡ በኢትዮጵያም የጥላቻ ንግግሮች የፈጠሩትን ማኅበራዊ መናጋት እና ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ምናልባት እንደ ደቡብ አፍሪካ በምጣኔ ሃብት ጠንከር ባንልም፣ ብሎም ራሱን የቻለ የእኩልነት ፍ/ቤት ማቋቋም ባይቻል ፤ ራሱን የቻለ የጥላቻ ንግግሮችን እና የማንንነት ጥቃትን የሚመለከት ችሎት ማቋቋም ተገቢ ይመስለኛል፡፡

 

ክፍል ሁለት … ይቀጥላል፡፡

Last modified on Wednesday, 16 September 2020 17:14
Yohannes Eneyew Ayalew

The blogger is a PhD Candidate at the Faculty of Law, Monash University, Melbourne in Australia. His project investigates the appropriate balance between freedom of expression and privacy on the internet under the African human rights system. Prior to joining Monash Law, Yohannes was a lecturer in law at School of Law, Bahir Dar University where he was teaching and researching on Media Law and Advanced Construction Law. He previously taught at the School of Law, Samara University in 2014 where he served as Assistant Lecturer. Later, he was appointed as—Lecturer in Law, and Head of the Law School. He holds a Master of Laws (LL.M) in International Human Rights Law (University of Groningen, the Netherlands), Honours Masters in Leadership (Groningen Honours College, the Netherlands), LL.M in Public International Law (Addis Ababa University) and Bachelor of Laws (LL.B) in Law (Wollo University). His research, teaching and publication focuses on—International Human Rights Law, International Humanitarian Law, Public International Law, Media Law, Internet Freedom, and Internet Intermediaries’. You can access his publications at ORCID. For any comment, reach him at T: +61402358901 E: eneyewyohannes@gmail.com and Twitter: @yeayalew.